Reading News & Blog

Let's talk about solution

User Rating: 0 / 5

Star InactiveStar InactiveStar InactiveStar InactiveStar Inactive

“ይቅርታ የሚለው ቃል ከፍተኛ ኃይል አለው። ይቅርታ መጠየቅ አለመግባባትን ያስወግዳል፤ በብሔራት መካከል የተፈጠረን ግጭት ያስቀራል፤ መንግሥታት የዜጎቻቸው ሥቃይ እንዲሰማቸው ያደርጋል እንዲሁም በወዳጆች መካከል ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖር ያደርጋል።

መጽሐፍ ቅዱስ ከልብ ይቅርታ መጠየቅ አብዛኛውን ጊዜ አንድን የሻከረ ግንኙነት ወደ ቀድሞው ሁኔታ ለመመለስ የሚያስችል ወሳኝ እርምጃ እንደሆነ ይገልጻል። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ ስለ አባካኙ ልጅ በተናገረው ምሳሌ ላይ ልጁ ወደ ቤቱ ተመልሶ አባቱን ከልቡ ይቅርታ በጠየቀ ጊዜ አባትየው እርሱን ለመቀበል ሙሉ በሙሉ ፈቃደኛ ነበር። (ሉቃስ 15:​17-24) አዎን፣ አንድ ሰው ኩራቱን ዋጥ አድርጎ ይቅርታ ለመጠየቅና ምህረት ለማግኘት ከመጣር ወደ ኋላ ማለት የለበትም። እርግጥ ነው፣ ከልባቸው ትሁት የሆኑ ሰዎች ይቅርታ መጠየቅ አይከብዳቸውም።

ይቅርታ መጠየቅ ያለው ኃይል

በጥንቷ እስራኤል ትኖር የነበረችው ብልኋ አቢግያ ይቅርታ የጠየቀችው ባሏ ለፈጸመው ስህተት ቢሆንም ይቅርታ መጠየቅ ያለውን ኃይል ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ምሳሌ ትታለች። ከጊዜ በኋላ የእስራኤል ንጉሥ የሆነው ዳዊትና ሎሌዎቹ በምድረ በዳ ሳሉ የአቢግያን ባል የናባልን መንጋ ይጠብቁለት ነበር። ይሁን እንጂ የዳዊት ሎሌዎች ናባልን ዳቦና ውኃ እንዲሰጣቸው በጠየቁት ጊዜ ሙልጭ አድርጎ ሰድቦ ባዶ እጃቸውን ሰደዳቸው። በንዴት የጦፈው ዳዊት በናባልና በቤተሰዎቹ ላይ ለመዝመት 400 ሰዎች አስከትሎ ሄደ። በዚህ ጊዜ ሁኔታውን የሰማችው አቢግያ ዳዊትን ለማግባባት ወጣች። ልክ እንዳየችውም እግሩ ላይ ተደፋች። ከዚያም “ጌታዬ ሆይ፣ ይህ ኃጢአት በእኔ ላይ ይሁን፤ እኔ ባሪያህ በጆሮህ ልናገር፣ የባሪያህንም ቃል አድምጥ” በማለት ተናገረች። በኋላም ሁኔታውን ካስረዳችው በኋላ የምግብና የመጠጥ ስጦታ አቀረበችለት። በዚህ ጊዜ ዳዊት “በደኅና ወደ ቤትሽ ሂጂ፤ እነሆ፣ ቃልሽን ሰማሁ፣ ፊትሽንም አከበርሁ አላት።”​—⁠1 ሳሙኤል 25:​2-35

አቢግያ ባሏ ላሳየው መጥፎ ጠባይ በትህትና ያቀረበችው ይቅርታ ቤተሰቧን ከጥፋት አድኖላታል። እንዲያውም ዳዊት ‘ደም ወደ ማፍሰስ እንዳይሄድ፤ በእጁም በቀል እንዳያደርግ’ ስለከለከለችው አመስግኗታል። ዳዊትንና ሎሌዎቹን የበደለችው እርስዋ ባትሆንም በቤተሰቧ ላይ የመጣውን ነቀፋ በመቀበል ከዳዊት ጋር እርቅ ፈጥራለች።

መቼ ይቅርታ መጠየቅ እንደሚገባ የሚያውቀው ሌላው ምሳሌ ደግሞ ሐዋርያው ጳውሎስ ነው። በአንድ ወቅት ሳንሄድሪን በተባለው የአይሁዳውያን ፍርድ ቤት ቀርቦ ለቀረበበት ክስ የመከላከያ ሐሳብ ማቅረብ ነበረበት። ጳውሎስ በሐቀኝነት በተናገራቸው ቃላት የተናደደው ሊቀ ካህናት ሐናንያ አፉን ይመቱት ዘንድ አጠገቡ የቆሙትን አዘዘ። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ “አንተ በኖራ የተለሰነ ግድግዳ፣ እግዚአብሔር አንተን ይመታ ዘንድ አለው፤ አንተ በሕግ ልትፈርድብኝ ተቀምጠህ ሳለህ ያለ ሕግ እመታ ዘንድ ታዛለህን?” አለው። ሁኔታውን ይከታተሉ የነበሩ ሰዎች ሊቀ ካህናቱን ተሳድበሃል በማለት ሲወቅሱት ሐዋርያው ጳውሎስ “ወንድሞች ሆይ፣ ሊቀ ካህናት መሆኑን ባላውቅ ነው፤ በሕዝብህ አለቃ ላይ ክፉ ቃል አትናገር ተብሎ ተጽፎአልና” በማለት ስህተቱን ያላንዳች ማንገራገር አምኗል።​—⁠ሥራ 23:​1-5

ጳውሎስ ፈራጅ ሆኖ የተሾመ ሰው ሕገ ወጥ ድርጊት መፈጸም የለበትም ብሎ መናገሩ ትክክል ነበር። ያም ሆኖ ለሊቀ ካህናቱ አክብሮት እንደሌለው በሚያስመስል መንገድ በመናገሩ ይቅርታ ጠይቋል።* ጳውሎስ ይቅርታ መጠየቁ ሸንጎው ሐሳቡን እንዲሰማ በር ከፍቷል። ጳውሎስ የሸንጎው አባላት እርስ በርስ የማይግባቡበትን ነጥብ ያውቅ ስለነበር በትንሣኤ ተስፋ በማመኑ የተነሳ ፍርድ ፊት መቅረቡን ተናገረ። በዚህ ምክንያት በፈሪሳውያንና በሰዱቃውያን መካከል ከፍተኛ ጠብ ተነሳ። ፈሪሳውያኑም ከጳውሎስ ጎን ቆሙ።​—⁠ሥራ 23:​6-10

ከእነዚህ ሁለት ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌዎች ምን እንማራለን? በሁለቱም ታሪኮች ከልብ በመነጨ ስሜት የቀረበው ይቅርታ ለተጨማሪ ውይይት በር ከፍቷል። ስለዚህ ይቅርታ መጠየቅ እርቅ ለመፍጠር ሊረዳ ይችላል። አዎን፣ ስህተታችንን ማመናችንና ይቅርታ መጠየቃችን ጠቃሚ ውይይት ለማድረግ የሚያስችል በር ይከፍትልናል።

‘ግን እኮ አንድም ስህተት አልሠራሁም’

በተናገርነው ወይም ባደረግነው ነገር ያሳዘንነው ሰው እንዳለ ከተገነዘብን ግለሰቡ ምክንያታዊ እንዳልሆነ ወይም ሆደ ባሻ እንደሆነ ይሰማን ይሆናል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን እንደሚከተለው በማለት መክሯቸዋል:- “እንግዲህ መባህን በመሠዊያው ላይ ብታቀርብ፣ በዚያም ወንድምህ አንዳች በአንተ ላይ እንዳለው ብታስብ፣ በዚያ በመሠዊያው ፊት መባህን ትተህ ሂድ፣ አስቀድመህም ከወንድምህ ጋር ታረቅ፣ በኋላም መጥተህ መባህን አቅርብ።”​—⁠ማቴዎስ 5:​23, 24

ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ወንድም እንዳስቀየምከው ተሰምቶት ይሆናል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥምህ እንዳስቀየምከው ቢሰማህም ባይሰማህም ሄደህ ‘ከወንድምህ ጋር መታረቅ’ ያለብህ አንተው ራስህ መሆንህን ኢየሱስ ተናግሯል። በግሪክኛው ጥቅስ መሠረት ኢየሱስ እዚህ ላይ የተጠቀመበት ቃል “ሁለት ሰዎች እርስ በርስ በሚጋጩበት ጊዜ ይቅር ተባብለው እርቅ መፍጠር እንዳለባቸው ያመለክታል።” (ቫይንስ ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኦልድ ኤንድ ኒው ቴስታመንት ወርድስ) በእርግጥም በሁለት ሰዎች መካከል አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜ በአለፍጽምና ምክንያት በሁለቱም ላይ ጥፋት መገኘቱ አይቀርም። ይህ ከሆነ ደግሞ እርስ በርስ ይቅር ተባብለው እርቅ መፍጠር ይኖርባቸዋል።

ዋናው ነገር ስህተተኛው ማን ነው የሚለው ሳይሆን እርቅ ለመፍጠር ቀዳሚውን እርምጃ የሚወስደው ማን ነው የሚለው ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ አንዳንድ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ገንዘብን በመሳሰሉ ጉዳዮች ስላልተስማሙ የእምነት ወንድሞቻቸውን በዓለማዊ ፍርድ ቤት እንዳቆሟቸው ሲገነዘብ “ብትበደሉ አይሻልምን? ብትታለሉስ አይሻልምን?” በማለት ገሥጿቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 6:​7) ጳውሎስ ይህንን የተናገረው ክርስቲያን ባልንጀሮቹ በመካከላቸው የተፈጠረውን አለመግባባት በዓለማዊ ፍርድ ቤት ለመፍታት ከመሞከር እንዲቆጠቡ ለማድረግ ቢሆንም ሊተላለፍ የተፈለገው ነጥብ ግልጽ ነው። ይበልጥ አስፈላጊው ነገር ስህተተኛውን መለየቱ ሳይሆን በክርስቲያኖች መካከል ሰላም መስፈኑ ነው። ይህንን መሠረታዊ ሥርዓት ማስታወሳችን እንዳስቀየምነው የተሰማውን ሰው ይቅርታ ለመጠየቅ ሁኔታውን ቀላል ያደርግልናል።

ከልብ የመነጨ መሆን ይገባዋል

ሆኖም አንዳንድ ሰዎች ይቅርታ የሚለውን ቃል ከልክ በላይ ይጠቀሙበታል። ለምሳሌ ያህል በጃፓን ይቅርታን ለመግለጽ የሚያገለግለው ሱሚማሰን የተባለ ቃል ተደጋግሞ ሲነገር ይሰማል። እንዲያውም ቃሉ አመስጋኝነትን ለመግለጽ የሚያገለግል ሲሆን ቃሉን የሚጠቀምበት ሰው ውለታውን ለመመለስ ባለመቻሉ የሚሰማውን የመሸማቀቅ ስሜት ያመለክታል። ቃሉ ተደጋግሞ ከመነገሩ የተነሳ አንዳንዶች ‘እንዲያው ሰዎች ይቅርታ የሚጠይቁት ከልባቸው ይሆን?’ ብለው ሊያስቡ ይችላሉ። በሌሎች ባሕሎችም ይቅርታን ለመግለጽ የሚያገለግሉት ቃላት ከመጠን በላይ ጥቅም ላይ ውለዋል።

በየትኛውም ቋንቋ ቢሆን ይቅርታ ከልብ በመነጨ ስሜት መጠየቅ ይኖርበታል። አነጋገራችንና የድምፃችን ቃና ያዘንነውና የተጸጸትነው ከልባችን መሆኑን ማሳየት ይኖርበታል። ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራ ስብከቱ ላይ ደቀ መዛሙርቱን ‘ነገር ግን ቃላችሁ አዎን አዎን ወይም አይደለም አይደለም ይሁን፤ ከነዚህም የወጣ ከክፉው ነው’ በማለት አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 5:​37) ይቅርታ ከጠየቅክ ከልብህ ይሁን! በምሳሌ ለማስረዳት ያህል:- በአንድ የአውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ሰዎች ዕቃቸውን ለማስመዘን ተሰልፈው ተራቸውን ይጠብቃሉ። የአንድ ሰው ሻንጣ ከኋላው ተሰልፋ የነበረችውን ሴትዮ ገፋ አደረጋት። በዚህ ጊዜ ሰውዬው ይቅርታ ጠየቀ። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ሰልፉ ሲንቀሳቀስ ሻንጣው እንደገና ሴትዮዋን ገፋ አደረጋት። አሁንም ሰውየው በአክብሮት ይቅርታ ጠየቀ። ይህ ሁኔታ ለሦስተኛ ጊዜ ሲደገም ከሴትዮዋ ጋር አብሮ የነበረ አንድ ሌላ ሰው ይቅርታው ከልብ ቢሆን ኖሮ ሻንጣው እንዳይገፋት ጥንቃቄ ያደርግ እንደነበር ነገረው። አዎን፣ ከልብ በመነጨ ስሜት የተጠየቀ ይቅርታ ስህተቱን ላለመድገም ቁርጥ ውሳኔ ማድረግን ይጠይቃል።

ይቅርታ የጠየቅነው ከልባችን ከሆነ የሠራነውን ስህተት ማመን፣ ምህረትን መለመንና ስህተቱን ላለመድገም የቻልነውን ያህል ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ተበዳዩም ቢሆን ንስሃ የገባውን ሰው ይቅር ለማለት ፈቃደኛ መሆን ይኖርበታል። (ማቴዎስ 18:​21, 22፤ ማርቆስ 11:​25፤ ኤፌሶን 4:​32፤ ቆላስይስ 3:​13) ሁለቱም ወገኖች ፍጽምና የጎደላቸው በመሆናቸው እርቅ ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት ሁልጊዜ ቀላል ይሆናል ማለት አይደለም። ቢሆንም ይቅርታ መጠየቅ የሻከረውን ግንኙነት ለማደስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል።

ይቅርታ መጠየቅ ተገቢ የማይሆንበት ጊዜ

ማዘናችንንና መጸጸታችንን መግለጽ ሌላውን ወገን የሚያጽናና እንዲሁም የሻከረውን ግንኙነት ለማደስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ቢሆንም አንድ ብልህ ሰው ይቅርታ መጠየቅ ተገቢ የማይሆንበት ጊዜ እንዳለም ይገነዘባል። ለምሳሌ ያህል ሁኔታው ለአምላክ ታማኝ መሆንን ይመለከታል እንበል። ኢየሱስ ክርስቶስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ‘ራሱን ዝቅ በማድረግ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እስከመሞት እንኳ የታዘዘ ሆኗል።’ (ፊልጵስዩስ 2:​8) ይሁን እንጂ ከመከራ ለመሸሽ ሲል ለእምነቱ ይቅርታ አልጠየቀም። በተጨማሪም ሊቀ ካህኑ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ የሆንህ እንደ ሆነ እንድትነግረን በሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ” ብሎ በጠየቀው ጊዜ በፍርሃት እየተንቀጠቀጠ ይቅርታ ከመጠየቅ ይልቅ “አንተ አልህ ነገር ግን እላችኋለሁ፣ ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ” በማለት በድፍረት መልሷል። (ማቴዎስ 26:​63, 64) ከሊቀ ካህናቱ ጋር እርቅ ለመፍጠር ሲል ለአባቱ ለይሖዋ አምላክ ያለውን ታማኝነት የማጉደል ሐሳብ ፈጽሞ ወደ አእምሮው አልመጣም።

ክርስቲያኖች ባለሥልጣኖችን ያከብራሉ። ይሁን እንጂ አምላክን ስለታዘዙ ወይም ወንድሞቻቸውን ስለወደዱ ይቅርታ መጠየቅ አያስፈልጋቸውም።​—⁠ማቴዎስ 28:​19, 20፤ ሮሜ 13:​5-7

ሰላምን የሚያደፈርስ ነገር አይኖርም

በዛሬው ጊዜ ከመጀመሪያው አባታችን ከአዳም በወረስነው አለፍጽምና ምክንያት ሁላችንም ስህተት እንሠራለን። (ሮሜ 5:​12፤ 1 ዮሐንስ 1:​10) አዳም ኃጢአት ውስጥ ሊወድቅ የቻለው በፈጣሪው ላይ በማመፁ ምክንያት ነበር። ይሁን እንጂ አዳምና ሔዋን ሲፈጠሩ ፍጹማንና ኃጢአት የሌላቸው ነበሩ። አምላክ የሰው ልጆችን እነርሱ ወደነበሩበት የፍጽምና ደረጃ ለመመለስ ቃል ገብቷል። ኃጢአትንና የኃጢአት ውጤት የሆኑትን ነገሮች በሙሉ ያስወግዳል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 15:​56, 57

ይህ ምን ማለት እንደሚሆን ገምት! የኢየሱስ ግማሽ ወንድም የነበረው ያዕቆብ የአንደበትን አጠቃቀም በተመለከተ ምክር ሲሰጥ “በንግግሩ የማይሰናከል ማንም ሰው ቢኖር እርሱ ሰውነቱን ሁሉ መቆጣጠር የሚችል ፍጹም ሰው ነው” ብሏል። (ያዕቆብ 3:​2 አ.መ.ት) ፍጹም ሰው ምላሱን መቆጣጠር ስለሚችል እንዳመጣለት በመናገሩ ምክንያት ይቅርታ መጠየቅ አያስፈልገውም። ‘ሰውነቱን ሁሉ መቆጣጠር ይችላል።’ ፍጹም የምንሆንበት ያ ጊዜ ምንኛ የሚያስደስት ይሆናል! በዚያን ጊዜ በሰዎች መካከል አለመግባባት እንዲፈጠር የሚያደርጉ እንቅፋቶች አይኖሩም። እስከዚያው ድረስ ግን ለተሠራው ስህተት ልባዊና ተገቢ የሆነ ይቅርታ መጠየቅ እርቅ በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል።

 

 

Add a comment

Get In Touch

Contact with me on opportunities


HIRE ME

Follow Me

Copyright © Dr. Nebiyu Lera Alaro, PHD 2024

Search