መግቢያ
ስብከት ማለት ምንድንው? ስብከት ማለት፥ በክርስቶስ ኢየሱስ ሞትና ትንሳኤ ስለተገኘው የኃጢአት ይቅርታና ደህንነት ለሰዎች የምሥራቹን ማወጅ ማለትነው፡፡ በተጨማሪም የተለያዩ ሰዎች ስለ ስብከት ምንነት የሚከተሉትን አስተያየቶች
ይሰጣሉ፡፡
ስብክት ማለት፥ አንድ ሰው ከእግዚአብሔር መልእክት ተቀብሎ ያንን የተቀበለውን መልእክት ለሰዎች ሲያስተላልፍ ነው፡፡ የእግዚአብሔርን እውነት ለሰዎች መስተላለፍና ማካፈል ነው፡፡
ሕይወቱ በመለኮታዊው እስትንፋስ የነቃና ህያው የሆነ አንድ ሰው እሱ ደግሞ በተራው ያንን ያገኘወን ህይወት ሰጪ መለኰታዊ እስትንፋስ ለሌላው ሲያስተላልፍና የተኛች ነፍስ እንድትነቃ ሲያደርግ ነው፡፡
የመጽሐፍ ቅዱስ ዕውነቶችን ለሰዎች ማስተላለፍና በባህሪያቸውና በሕይወታቸው ለውጥ እንዲታይ ማድረግ ነው፡፡
ሆሜሌቲክስ(Homiletics)
የስብከት አዘገጃጀትና አቀራረብ በስነ መለኮት ትምህርት “ሆሜሌቲክስ”(Homiletics) በመባል ይታወቃል፡፡ “ሆሜሌቲክስ” (Homiletics) የሚለው የእንግሊዘኛ ቃል የመጣው “Homilia” ከሚለው የግሪክ ቃል ሲሆን ትርጉሙ “ንግግር” ማለት ነው፡፡ ለህዝብ የሚቀርብ ማንኛውም ዓይነት ንግግር ስበት እንዲኖረው ካስፈለገ በታላቅ ጥንቃቄና ጥበብ መዘጋጀት አለበት፡፡ ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ ሰዎች፣ ሌሎችም ጥሩ ተናጋሪ ለመሆን፤ የተለያዩ ስልጠናዎች ይወስዳሉ፡፡ ላቀራረባቸውም ጥንቃቄ ያደርጋሉ፡፡ ሃሳብ በተሳካ ቃላትና በጥሩ አቀራረብ ሲቀርብ
መንግሥትን እንኳን ሳይቀር ለማቋቋምም ሆነ ለማፍረስ እንደሚያስችል በፖለቲካው ዓለም ሲከሰት ተመልክተናል፡፡
አንድ ሰው በሕዝብ ፊት ቆሞ የሚናገረው ነገር ካልተደመጠለት ሃሳቡም ለሰዎች የማይገባ ከሆነ የዚያ ሰው ድካም ከንቱ ነው፡፡ ንግግር ሁሉ ማስተማር፡ ማድመጥም ሁሉ መማር አይደለም፡፡ ስለዚህ ለመደመጥና ለማስተማር እንድንችል የሚያበቃና የሚጠቅም ሥልጠና መውስድ ለሚናገርና ለሚያስተምር ሰው ሁሉ አስፈላጊ ነው፡፡
ሆሜሌቲክስ የስብከት ዝግጅትና አቀራረብን የሚያስተምር ጥበብ ነው፡፡ ጥሩ ዝግጅትና አቀራረብ ስብከትን ተደማጭነት እንዲኖረው ያደርጋል፡፡ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የምድር አገልግሎትም ስብከት መካከለኛ ሥፍራ የያዘ ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራዎች፣ በወንዞች፣ በምኩራቦችና ዕድሉን ባገኘበት ስፍራ ሁሉ የመንግሥትን ወንጌል እንደ ሰበከ በወንጌሎች ውስጥ እንመለከታለን፡፡ በሉቃስ ወንጌል ውስጥ እንደተጻፈው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ያገልግሎቱን ዓላማ ሲገልጽ ስብከት ባገልግሎቱ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ እንደያዘ ግልጽ አድርጎታል፡፡ “የጌታ መንፈስ
በእኔ ላይ ነው ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና ለታሰሩትም መፈታትን፣ ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ የተጠቁትንም ነፃ አወጣ ዘንድ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እስብክ ዘንድ ልኮኛል፡፡”(ሉቃስ 4፡ 18-19)
በመጨረሻም ስራውን ጨርሶ ከዚህ ዓለም ሊሄድ ሲል ለደቀመዛሙርቱ ትዕዛዝ ሲሰጣቸው እንዲህ ብሏል፡፡ “ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ።” (ማርቆስ 16፥15)እነዚህን ከመሳሰሉት ጥቅሶች መረዳት
እንደምንችለው ስብከት በቤተክርስቲያን ሕይወት ውስጥ መካከለኛ ቦታ እንዳለው ነው፡፡ የእግዚአብሔርን የምሥራች ወንጌል የምናውጀው በስብከት ነው፡፡ ስብከት ተራ ንግግር ሳይሆን በሰዎች ነፍስ ላይ ያተኰረ ሥራ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ አናጢ የሚሰራውን ሥራ በጥንቃቄ ባይሰራ የሚሰራውን ቤት ያበላሻል፡፡ ነገሩ የሚመረጥ ባይሆንም አንድ አናጢ ስራውን በጥንቃቄ ባይሰራ የሚያበለሸው የሰራውን ቤት ብቻ ነው፡፡ አናጢ ሲሰራ ያበላሸውን ቤት አፍርሶ እንደገና የመሥራት ዕድል አለው፡፡ የሰባኪ ሥራ ግን ከሰው ህይወት ጋር በቀጥታ የተያያዘ ስለሆነ ስራውን በጥንቃቄና በማስተዋል መስራት አለበት፡፡ ሰባኪ እንደ አናጢው ያበላሸውን ለማፍረስና እንደገና ደግሞ ያንኑ መልሶ የመስራት ዕድል የለውም፡፡ ሰባኪ የሚሰራውን በትክክሉ ለመሥራት አስቀድሞ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባዋል፡፡ የስብከት አዘገጃጀትና አቀራረብ (የሆሜሊቲክስ) ትምህርትና ሥልጠና ለሰባኪዎች የሚያስፈልገውም ለዚህ ነው፡፡